‹‹ሁሉም የሠው ልጆች እኩል ፍጡራን ናቸው›› የአሜሪካኑ ሦስተኛ መሪ ቶማስ ጄፈርሰን ይህን ከተናገረበት ዘመን ከ104 ዓመታት በኋላ በርግጥም አባባሉ ትክክል ስለመሆኑ ሕያው ምስክር የሆነች ድንቅ እንስት ወደዚህች ዓለም ተቀላቀለች፡፡ የሠውን እኩልነት በተግባር ኖራ ያሳየች፤‹‹በዓለም ላይ ደስታ ብቻ ቢኖር ጀግንነትን አንማርም ነበር›› በማለት ችግርና ፈተናን ወደ ዕድል የቀየረች ይህች ጀግና ሴት ድንቅ ፀሐፊ፣ የመብት ተሟጋች እና ፖለቲከኛም ጭምር ነበረች፡፡ ሄለን አዳምስ ኪለር። ብዙ ወዳጅ ዘመዶቿና ጓደኞቿ ስለብርቱነቷ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ‹‹እኛ የምናይና የምንሰማውን እንኳ ማየት እና መስማት ሳትችል ትታዘበን ነበር፡፡›› ሲሉ አድናቆታቸውን ይቸሯታል፡፡ ከእርሷ ጋር የነበራቸውን ገጠመኝ ሲያወሱም ‹‹በተለያየ ምክንያት ወጥተን ስንመለስ ‹‹ምን አያችሁ?›› ብላ ትጠይቃለች፡፡ የብዙዎቻችን መልስ ‹‹ምንም አዲስ ነገር የለም›› ነው፡፡ ሃሳቧን በግልጽ የማራመድ የመንፈስ ነፃነት የተቸራት ሄለን ታዲያ ይህን ምላሽ ስትሰማ ‹‹እኔኮ አንዲት ቅጠል ዳስሼ ብዙ ማለት እችላለው›› በማለት ነገሮችን ለመመልከት ለሠው ልጆች የተሰጠው አንዱ የሥሜት ሕዋስ ከሆነው ዓይን በላይ ልቦና እንደሚመለከት በተግባር ታሳያለች፡፡ አንድ ሆና ብዙ፣ ያኔ ኖራ በስራዋ እስከዛሬ ያለችው ሄለን አዳምስ ኪለር ውልደቷ ዘመናዊነትና ስልጣኔ ባልተስፋፋበት ዘመን እ.አ.አ በ1880 ከዛሬ 140 ዓመት በፊት ነበር። ከተወለደች ከዓመት ከስድስት ወር በኋላ ማየትም ሆነ መስማት ተሳናት፡፡ ምንም እንኳ ሕፃናት ሁሉን ለማወቅ በሚጓጉበት ዕድሜዋ ማየትና መስማት ቢሳናት አይኖቿ ሳያዩ፣ ጆሮዎቿ ሳይሰሙ፤ባልሰለጠነው ዓለምና ዘመን የሰለጠነች፤ዓለምን በልበ ብርሃንነቷ የተመለከተችና ያደመጠች ስለመሆኗ ሥራዎቿና በቅርብ የሚያውቋት ሁሉ ይመሰክሩላታል፡፡ ሄለን ኪለር ስለ ራሷ እንዲህ ትላለች ‹‹በህይወት ውስጥ ምርጥ እና እጅግ ውብ የሆኑት ነገሮች በዓይን አይታዩም፣ በእጅ አይዳሰሱም ይልቁንም በልቦናችን ብቻ የሚሰሙ ናቸው››፡፡ “story of my life” ከተሰኘው መጸሀፏ ጀምሮ ሌሎች ደርዘን የሚደርሱ መፀሀፎችን ለንባብ ያበቃችው ይህች ድንቅ የተፈጥሮ መገለጫ ስለ አካል ጉዳተኞች መብት ተሟግታለች፤ አስተምራለች፡፡ በአሜሪካ ፓለቲካ ውስጥም የሶሻሊስት ፓርቲ አባል በመሆን በቅስቀሳና በጽሁፍ ስራዎቿ አገልግላለች፡፡ባበረከተቻቸው ጉልህ አስተዋፅዖዎችም እ.አ.አ በ1964 በአሜሪካ የከፍተኛ የክብር ሽልማት የሆነውን ‹‹medal of freedom›› ከወቅቱ ፕሬዚንዳንት ሊንደን ጀንሰን ተቀብላለች። ሄለን ሀርቫርድ ዩንቨርስቲን በ20 ዓመቷ ተቀላቅላ የመጀመሪያ ዲግሪዎን አግኝታለች፡፡ በስራዎቿም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተቀብላለች። ሄለን ብዙዎችን ከሚያሰገርሙ ነገሮቿ ውስጥ አንዱ ሆኖ የሚነሳው እንግሊዘኛን፣ ግሪክኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛና ላቲንኛ ቋንቋዎችን በብሬል ማንበብ መቻሏ ነው፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ላይ አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግ የምትታወቀውና የጥንካሬ ተምሳሌት የሆነችው ይህች ሴት የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲከበር ትሞግትም ነበር፡፡ስለ ስራዎቿም እንዲህ ትላለች ‹‹ችግርን መሸሽ ችግርን ከመጋፈጥ የተሻለ አይደለም›› በዚህም ችግሮቿን ተጋፍጣ የአሸናፊነትን ድል መቀዳጀት በመቻሏ ለብዙዎች ፋና ወጊና ፈር ቀዳጅ ሆናለች፡፡ ‹‹አንተነትህን መቼም ቢሆን አትስበር ቀና ብለህ ኑር›› የምትለው ሄለን በፈተናዎች ሳትበገር ለማየቷ ምልከታዎን ሳያግደው፤አለመስማቷ ማዳመጧን ሳይከለክላት 87 ዓመታትን በሕይወት ከራሷ አልፋ ለሌሎች ኖሯ አሳልፋለች፡፡ እ.አ.አ 1968 በአንዱ ምሽት ግን ካሸለበችበት ዳግም አልነቃችም፡፡ ዘመኗን ብዙዎች ሊያደርጓቸው የማይደፍሯቸውንና የአይቻልምን መንፈስ ሰብራ ለሌሎች ብርሃን ሆና ዳግም ላትመለስ ይችን ዓለም ተሰናብታለች።
Add comment