እንደ አሁኑ የትምህርት ጠቀሜታ ባልሰረጸበት፤ሴት ልጅ ከማግባትና ከመውለድ የዘለለ ሚና እንደነበራት ከግንዛቤ ባልገባበት ወቅት፤ ወላጆቻቸው ለትምህርት ትልቅ ቦታ ነበራቸውና ገና በአራት ዓመታቸው ነበር ወደ አስኳላ የገቡት፡፡ የመጀመሪያውን መንፈቀ ዓመት ትምህርት ሊያገባድዱ በተቃረቡበት ወቅት ታዲያ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ከትምህርት ገበታቸው ተለቀው ወደቤታቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር ከየት እንደመጣ ያላወቁት የበግ መንጋ መሀል አንዱ በግ ያሯሩጣቸው የጀመረው. ዛሬ ላይ በቅጡ ባያስታውሱትም ለጨዋታ ይሁን የፍራቻ አልያም ከበጎቹ መሀል ያሯሯጣቸውን በግ ሽሽት ባደረጉት ሩጫ ከመሬት የወደቀ የአጥር ሽቦ አጠገብ ራሳቸውን ወድቀው ያገኙታል.
ስለ ሁኔታው የሰሙት ቤተሰቦቻቸው ከተባለው ስፍራ ሲደርሱ የልጃቸው ቀኝ ዓይን በበጉ ይሁን በአጥር ሽቦው ተወግቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከመሬት ተንጋለው ሲቃ እያሰሙ ያገኟቸዋል፡፡ ልጃቸውን ለማሳከምም ከአዲስ አበባ አልፈው ብዙ ተጉዘዋል፡፡ ጣልያናዊያን የሕክምና ባለሞያዎችና የተሻለ ሕክምና ወደነበረበት የኤርትሪያ ዋና ከተማ ኣስመራ ድረስ በመጓዝም የበርካታ ሆስፒታሎችን በር አንኳክተዋል፡፡
አባታቸው በልጃቸው ቀኝ ዓይን ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ እንዲወጣ ቢጠይቁም ለማደንዘዣ የጠነከረ ገላ ስላልነበራቸው 12 ዓመት ሲሆናቸው መልሰው እንዲያመጧቸው ከሕክምና ባለሞያዎቹ ምላሽ ይሰጧቸዋል፡፡ ነገር ግን ከዓመት በኋላ ጉዳቱ ተዛምቶ የግራ ዓይናቸውም ዕይታውን አጣ፡፡ ይህንን የተመለከቱ ቤተሰቦቻቸውም የልጃቸው ዓይን መዳን ላይ ተስፋ በመቁረጥ ሰበታ መርሀ ዕውራን ትምህርት ቤት አስገቧቸው፡፡
ከቆይታ በኋላ ደግሞ የመስማት ችሎታቸውን እንዳጡ የሚያስታውሱት የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር መስራችና ዋና ዳይሬክተር ሮማን መስፍን ለችግሮችመፍትሔው ማዘን ሳይሆን የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን ተቋቁሞ ወደ ስኬት የመለወጥ ብቃትን ማዳበር ነው ይላሉ፡፡
Leave a reply