ከታኅሳስ 5 እስከ ታኅሳስ 11 ከተከናወኑ አገራዊ ታሪካዊ ክስተቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን ከስልጣን ለማስወገድ የተጠነሰሰው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ክስተት በተለምዶ ‹‹የታኅሳስ ግርግር›› በመባል ይታወቃል፡፡ ከመፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾቹ መካከል ጎልተው የሚጠቀሱት ወንድማማቾቹ ብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ (የክብር ዘበኛ ጦር አዛዥ) እና ግርማሜ ነዋይ ናቸው፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተጀመረው ታኅሳስ 4 ቀን 1953 ዓ.ም ሲሆን በወቅት ንጉሰ ነገሥቱ ለጉብኝት ወደ ብራዚል ሄደው ነበር፡፡
ታኅሳስ 5 ቀን 1953 ዓ.ም – የመፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾቹ ዓላማቸውን ይፋ አደረጉ። ለውጥ ፈላጊ ናቸው የሚባሉትን ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሾማቸውንና አልጋ ወራሹን አስፋ ወሰንን (‹‹አስገድደው››) በማስማማትም መንግሥት በቆረጠላቸው ደመወዝ እየተዳደሩ ለሕገ መንግሥት የሚገዙ ንጉሥ ሆነው እንደሚያገለግሉ እራሳቸው ለሕዝቡ በሬዲዮ እንዲያስተላልፉ አደረጉ።
Add comment