እንደምን ሰነበታችሁ ውድ አንባቢያን! በዛሬው የ‹‹ተምሳሌት›› አምድ የምናስቃኛቸሁ ለጥንታዊ ግሪክ እንዲሁም ለአውሮፓ ስነ-ጽሑፍ መሰረት ናቸው የሚባሉት የ‹‹ኢሊያድ›› እና ‹‹ኦድይሴይ›› ግጥሞች ጸሐፊ ስለሆነው ስለዓይነስውሩ ባለቅኔ ሆሜር ነው፡፡
ሆሜር የተወለደበትን ትክክለኛ ጊዜ መናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆሜር የኖረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በመሆኑ የታሪክ ጸሐፊዎች ስለልደቱ በጽሑፍ ያስቀመጧቸው ጊዜያት የተለያዩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች ‹‹ኢሊያድ›› የተሰኘው የሆሜር ግጥም ስለ ትሮጃን ጦርነት (Trojan War) የሚተርክ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሆሜርን የልደት ዘመን ከ1200 እስከ 900 ዓመተ ዓለም ባለው ጊዜ ውስጥ ሲያደርጉት፤ ሌሎች የታሪክ አጥኚዎች ደግሞ የአፃፃፉ ስልት የቅርብ ጊዜ እንደሆነ በማስረዳት ሆሜር ከ800 እስከ 750 ዓመተ ዓለም ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተወለደ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ ‹‹የታሪክ አባት›› በመባል የሚታወቀው ግሪካዊ ሄሮዶተስ በበኩሉ፣ ሆሜር በ850 ዓመተ ዓለም አካባቢ ስለመወለዱ ጽፏል፡፡
ስለትውልድ ዘመኑ ብቻም ሳይሆን የትውልድ ስፍራውም ሁሉንም የታሪክ አጥኚዎችን ሊያስማማ አልቻለም፡፡ እስካሁን ድረስም ሰባት የዓለም አካባቢዎች (ከተሞች) የሆሜር የትውልድ ስፍራ እንደሆኑ በየፊናቸው አውጀዋል፡፡ ‹‹ኢሊያድ›› እና ‹‹ኦድይሴይ›› ግጥሞች ውስጥ ከሰፈሩት ገለፃዎች በመነሳት ሆሜር ‹‹ኤዥያ ማይነር›› ተብሎ በሚታወቀውና በእስያ በኩል በነበረው የጥንታዊት ግሪክ ክፍል ውስጥ እንደተወለደ በብዙ የታሪክ ድርሳናት ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህ የሆሜር የትውልድ ስፍ ነው ተብሎ የሚታመነው ስፍራ በአሁኑ ወቅት ቱርክ የምትገኝበት አካባ ነው፡፡
የታሪክ ጸሐፍት የባለቅኔው ሆሜርን ዓይነ ስውርነት የሚተርኩት ከቅኔዎቹ ትርጓሜ በመነሳት ነው፡፡ ብዙዎቹ ጸሐፊዎች ‹‹ዓይነ ሰውር እንዲሁም ፂምና የተጠቀለለ ፀጉር ያለው›› በማለት ስለሆሜር አካላዊ ገጽታ በመጽሐፎቻቸው ተርከዋል፡፡
15ሺ 693 ሄክሳሜትር (የግጥም ስንኝ መስመር) ያሉት ‹‹ኢሊያድ›› የተሰኘው የሆሜር ግጥም በ24 መጽሐፍት ተከፋፍሎ የተፃፈ ነው፡፡ ግጥሙ ‹‹የኢሊዮን መዝሙር›› እና ‹‹የኢሊየም ዘፈን›› በሚሉ ሌሎች ስያሜዎቹም ይታወቃል፡፡ ግጥሙ የተፃፈው በትሮጃን ጦርነት (Trojan War) ወቅት እንደሆነ ይታመናል፡፡ የትሮጃን ጦርነት የግሪክ ግዛተ ዐፄዎች የትሮይ ከተማን ለ10 ዓመታት ያህል በመክበብ ያደረጉት ጦርነት ነበር፡፡ ግጥሙ ስያሜውን ያገኘው ‹‹ኢሊየም›› ከተሰኘው የትሮይ ከተማ ሌላ መጠሪያ ነው፡፡ በግጥሙ ውስጥ ስለትሮጃን ጦርነት በስፋት መገለፁ ግጥሙ የተፃፈው በጦርነቱ ወቅት ነው ተብሎ እንዲታመን ምክንያት ሆኗል፡፡
‹‹ኦድይሴይ›› 12ሺ901 ሄክሳሜትር ስንኞች ያሉት ሲሆን ከትሮጃን ጦርነት መካሄድ በኋላ እንደተፃፈ ይታመናል፡፡ ግጥሙ ኦድይሰስ የተባለው የግሪክ የጦር ጀግና የትሮጃንን ጦርነት አሸንፎ ሲመለስ ስላጋጠመው አሳዛኝ ገጠመኝ የሚተርክ ነው፡፡ ‹‹ኦድይሴይ›› የተባለው የግጥሙ ስያሜ የተወሰደውም ከጦሩ ጀግና ከኦድይሰስ ነው፡፡
ሆሜር በግጥሞቹ ውስጥ ግሪኮችን ‹‹አኬያንስ›› እያለ ይጠራቸዋል፡፡ ‹‹ኢሊያድ››ና ‹‹ኦድይሴይ›› ስለጦርነት ወቅትና ከጦርነት በኋላ ስለነበረ ጊዜ የተፃፉ በመሆናቸው የአፃፃፍ ስልትና የስሜት ልዩነት ይንፀባረቅባቸዋል፡፡ ይህም ብዙ የታሪክና የስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ሁለቱ ግጥሞች በአንድ ሰው የተፃፉ አይደሉም የሚል ክርክር እንዲያነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡
‹‹ኢሊያድ›› እና ‹‹ኦድይሴይ›› የተባሉት ግጥሞች ለጥንታዊ ግሪክ ስነ-ጽሑፍ መሰረት ከመሆናቸው ባሻገር በምዕራቡ ዓለም የባህልና ኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች እንደሆኑ በብዙ ባለሙያዎች ተመስክሮላቸዋል፡፡ ስራዎቹ ዛሬም ድረስ በብዙ የታሪክና የስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ጥናት ይደረግባቸዋል፡፡
የታሪክ ጸሐፊዎችን የሚስማማ ባሆንም ሆሜር ከ‹‹ኢሊያድ›› እና ከ‹‹ኦድይሴይ›› በተጨማሪ የሌሎች ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ የስነ-ጽሑፍ ስራዎች ባለቤት እንደሆነም ይነገራል፡፡
Add comment