ግንቦት 30 ቀን 1874 ዓ.ም – በግዛት ይገባኛል ምክንያት የተጣሉት ንጉሥ ምኒልክ (ንጉሰ ሸዋ) እና ንጉሥ ተክለሃይማኖት (ንጉሰ ጎጃም) እምባቦ በተባለ ስፍራ ላይ ተዋግተው የንጉሥ ምኒልክ ጦር ባለድል ሆነ፡፡ ንጉሥ ምኒልክ በጦርነቱ ላይ ቆስለው የተማረኩትን ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ቁስላቸውን እያጠቡ አስታመው አዳኗቸው፡፡ ከጦርነቱ የተረፈውን የጎጃም ጦርም ስንቅ ሰጥተው ወደአካባቢው ሸኙት፡፡
የጎዣሙ ንጉሥ ከዳኑ በኋላም ንጉሥ ምኒልክ ‹‹ተክለሃይማኖት፣ አንተ ብትማርከኝ ምን ታደርገኝ ነበር?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ‹‹ለምን እዋሽሃለሁ እገድልህ ነበር! አንተ ግን እንደ እናት ነህ፤ አንተ’ማ እምዬ ነህ!›› ብለው መለሱላቸው፡፡
ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም – አንጋፋው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ተመሰረተው (ሕትመት ጀመረ)፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከስደት ተመልሰው ዙፋናቸው ላይ ከተቀመጡ ከአንድ ወር በኋላ፣ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የረዳትነቱን ስራ ይሰራ ዘንድ ተመሰረተ›› ብለው የጋዜጣውን ምስረታ አበሰሩ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር ‹‹ ‹‹ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ስራ ይጀመራል፡፡ ይህ ቀን ላዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው›› ብለው በተናገሩት መሰረት ጋዜጣው ‹‹አዲስ ዘመን›› ተብሎ ተሰየመ፡፡
ጋዜጣው እነበዓሉ ግርማን፣ ጳውሎስ ኞኞን፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን፣፣ ዘነበ ወላን፣ ደምሴ ፅጌን፣፣ ስብሓት ገብረእግዚአብሔርንና ሌሎች ታላላቅ ጋዜጠኞችንና ደራሲያንን ያፈራ አንጋፋ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም አንጋፋ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችና ደራሲያን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በኩል ያለፉ ናቸው፡፡
አንባቢ ማኅበረሰብን በመፍጠር፣ የጋዜጠኝነት ሙያን በማሳደግ፣ ጠንካራ ጸሐፊዎችን በማፍራት፣ የታሪክ መዝገብ በመሆንና ሌሎች ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ አስተዋፅኦዎችን በማበርከት ረገድ ጉልህ ሚና ያለው ይህ አንጋፋ ጋዜጣ፣ በየጊዜው ስልጣን የሚጨብጡ ገዢዎች የራሳቸውን ተልዕኮ ማስፈፀሚያ እያደረጉት፣ አንዱ ወድቆ ሌላው ሲተካ ቀድሞ ያመሰገነውን መልሶ ሲወቅስ፣ አንዳንድ ጊዜም የሚያስደምሙ ዘገባዎችን ሲያቀርብ …. እንዲህ እንዲህ እያለ ጉዞውን ቀጥሎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ አንጋፋ ጋዜጣ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ፣ ለ80 ዓመታት ያህል ሕትመቱ ሳይቋረጥ፣ እስከዛሬ ድረስ በአማርኛ እየታተመ ለአንባቢያን በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡
ሰኔ 1 ቀን 1806 ዓ.ም – የንጉሰ ነገሥት የዳግማዊ አጤ ምኒልክ አያት የሆኑትና የልጅ ልጃቸው ምኒልክ አዲስ አበባ ላይ ከተማ እንደሚመሰርቱ ትንቢት የተናገሩት ታላቁና ስመ ጥሩ የሸዋ ንጉሥ፣ ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የሸዋ ንጉሥ ሆነው ነገሱ፡፡
ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የራስ ወሰንሰገድ አስፋወሰን እና የወይዘሮ ዘነበወርቅ ጎሌ ልጅ ናቸው፡፡ በዘመኑም ‹‹ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሚገዛ ምኒልክ የሚባል ንጉሥ ይነግሣል›› የሚባል ንግርት ስለነበር፣ አባታቸው ራስ ወሰንሰገድ ‹‹ምኒልክ›› የሚል ስም አውጥተውላቸው ነበር።
አባታቸው ራስ ወሰንሰገድ ሲሞቱ በ18 ዓመታቸው የአባታቸውን አልጋ ወርሰው ሸዋን መግዛት ጀመሩ፡፡ ንጉሥ ሳህለሥላሴ ከሸዋ ባላባቶች መካከል (ከነጋሲ ክርስቶስ እስከ ኃይለመለኮት ድረስ ካሉት ገዢዎች መካከል) ኃያሉ፣ ሰፊ ግዛትና ብዙ ሀብት የነበራቸው እንደሆኑ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ በወቅቱ በዓለም ላይ ኃያላን ከነበሩት ከብሪታኒያና ከፈረንሳይ መንግሥታትም ጋር የንግድና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸውም የዚሁ ኃያልነታቸው ማሳያ ነው፡፡
‹‹አንቺ ቦታ የልጅ ልጄ ትልቅ ከተማ ይቆረቁርብሻል›› ብለው ስለ አዲስ አበባን ትንቢት እንደተናገሩም በታሪክ ላይ ተጽፏል፡፡ ከእርሳቸው ሞት በኋላም ልጃቸው ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ እና የልጅ ልጃቸው ምኒልክ ኃይለመለኮት ነግሰው ሸዋን ገዝተዋል፡፡ ንጉሥ ሳህለሥላሴ እንደተነበዩትም አዲስ አበባ በዳግማዊ አጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተቆረቆረች፡፡
ሰኔ 1 ቀን 1916 ዓ.ም – በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የሆኑት መንግስቱ ለማ ተወለዱ። መንግስቱ ለማ በመንፈሳዊው ዘርፍ እስከ ቅኔ የተማሩ ሲሆን በዓለማዊው ደግሞ ለንደን ድረስ ተጓዘው ዩኒቨርሲቲ በመግባት የፖለቲካ ሳይንስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ተከታትለዋል።
መንግስቱ ለማ በርካታ የስነ ጽሑፍ ሥራዎች ያሏቸው ሲሆን በተለይ በግጥም እና በተውኔት ጽሑፍ የጎላ አበርክቶ አድርገዋል። ‹‹የግጥም ጉባኤ››፣ ‹‹የአባቶች ጨዋታ››፣ ‹‹ባሻ አሸብር በአሜሪካ›› የተባሉት መጽሐፍት ከግጥም ስብስቦቻቸው ተጠቃሽ ሲሆኑ ዘመናዊ ኮሜዲን ለሀገራችን ያስተዋወቁባቸው ‹‹ጠልፎ በኪሴ››፣ ‹‹ያላቻ ጋብቻ››፣ ‹‹ባላካባና ባለዳባ››፣ ‹‹ፀረ ኮሎኒያሊስት››፣ ‹‹የዓለሙ ንጉሥ›› እና ‹‹ሹሚያ›› ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያስገኙላቸው የተውኔት ጽሑፎቻቸው ናቸው። ስራዎቻቸውም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅትንና የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ሥነ ጽሑፍ ሽልማቶችን ጨምሮ ሌሎች እውቅናዎችን እንዲያገኙ አስችለዋቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውኔት አፃፃፍ ዘዴን ሲያስተምሩ ዘመናዊውን አፃፃፍ ከባህላዊው ጋር በማዋሃድ ለተማሪዎቻቸው አዲስ የአፃፃፍ ስልት አስጨብጠዋል፡፡ ሊቁን አባታቸውን አለቃ ለማ ኃይሉን 45 ሰዓታትን የፈጀ ቃለ መጠይቅ በማድረግ የቃል አጣጣላቸውን የአነጋገር ለዛቸውን ጠብቀውላቸው የዘጠና አምስት ዓመታት የሕይወት ታሪካቸውን እያብራሩ ስርዓት አስይዘው ‹‹መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ›› በሚል ርዕስ በ1959 ዓ.ም አሳትመውላቸዋል፡፡ ባለቅኔውና ገጣሚው መንግሥቱ ለማ ሐምሌ 21 ቀን 1980 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡
ሰኔ 5 ቀን 1956 ዓ.ም – የፀረ-አፓርታድ ንቅናቄ መሪው ኔልሰን ማንዴላና ሰባት ጓዶቻቸው የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው፡፡ ማንዴላ ከ27 ዓመታት እስራት በኋላ ከእስራት ተፈትተው፤ ምርጫ አሸንፈው የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝደንት እንዲሁም የ1985 ዓ.ም የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡
Add comment