ግንቦት 23 ቀን 1906 ዓ.ም – አልጋወራሽ ልጅ ኢያሱ አባታቸውን ራስ ሚካኤል አሊን የወሎና የትግራይ ንጉሥ አድርገው አነገሷቸው፡፡ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም በጃን ሜዳ ታላቅ ስብሰባ ተደርጎ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ፣ እጨጌ ወልደጊዮርጊሥ፣ ራሶች፣ ደጃዝማቾች፣ ሚኒስትሮችና የውጭ አገር መንግሥታት ተወካዮችና መልዕክቶኞች በተገኙበት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የልጃቸው ልጅ፣ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ወራሻቸው መሆናቸውን ያሳወቁበት ቃል/አዋጅ በይፋ ተነገረ፡፡ ልጅ ኢያሱም በጊዜው ገና 13 ዓመት እንኳ ስላልሞላቸው ራስ ተሰማ ናደው ሞግዚት ሆነው ተሾሙለት፡፡
ንጉሰ ነገሥቱም ከ1903 ዓ.ም ጀምሮ በፅኑ ሕመም ተይዘው ስለነበር አልጋወራሹ በሞግዚታቸውና በመኳንንቱ በመታገዝ አገር ‹‹የማስተዳደር›› ስራቸውን ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ሞግዚታቸው ራስ ተሰማ ናደው በዚያው ዓመት (በ1903 ዓ.ም) ሞቱ፡፡ ከራስ ተሰማ ሞት በኋላም መኳንንቱ የአልጋ ወራሹ ሞግዚት ሆነው በአቋራጭ ንግሥናውን ለማግኘት ሲሉ ይሻኮቱ ጀመር፡፡ አልጋወራሹም ‹‹ከእንግዲህ ሞግዚት አያስፈልገኝም፤ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን የማስተዳደሩን ስራ ብቻዬን እወጣዋለሁ›› አሉ፡፡ ልጅ ኢያሱም ‹‹ፈረሴ የቀይ ባሕርን ውሃ ሳይጠጣ ዘውድ አልጭንም›› ብለው ከንግሥናው ይልቅ ሌሎች ተግባራት ላይ አተኮሩ፡፡
ግንቦት 23 ቀን 1906 ዓ.ም የወሎ ገዢ የነበሩትን አባታቸውን ራስ ሚካኤልን የወሎና የትግራይ ንጉሥ አድርገው አነገሷቸው፡፡ ይህ ንግሥና ‹‹ስልጣን ከእጃችን እንዲወጣ በር ይከፍታል›› ብለው የሰጉት የሸዋ መኳንንት በልጅ ኢያሱ ላይ በርካታ ክሶችን አዘጋጅተው፣ ‹‹የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ልጅ ዘውዲቱ ምኒልክን አንግሰናል፤ የራስ መኮንን ወልደሚካኤል ልጅ የሆኑትን ተፈሪ መኮንንን ደግሞ አልጋ ወራሽ አድርገናል›› ብለው መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የልጅ ኢያሱን ከስልጣን መሻር ይፋ አደረጉ፡፡
ግንቦት 24 ቀን 1972 ዓ.ም – CNN የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭቱን ጀመረ፡፡ ዋና መስሪያ ቤቱ አትላንታ፣ አሜሪካ ውስጥ የሆነው ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ፤ ከዓለም ታላላቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ የመገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ ነው፡፡
ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም – የፊደል ገበታ አባት ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ አረፉ፡፡ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ የፊደል ገበታ በማዘጋጀት በርካታ ኢትዮጵያውያን ከፊደል ጋር እንዲተዋወቁ ያደረጉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ በ1921 ዓ.ም. ማተሚያ ቤት በማቋቋም ‹‹እውቀት ይስፋ፤ድንቁርና ይጥፋ፤ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ›› የሚለውን ኃይለ ቃል አርዕስት በመስጠት ፊደልን፣ ፊደለ ሐዋርያንና አቡጊዳን በሦስት ረድፎች እያዘጋጀ በማሳተም በመላ ኢትዮጵያ ማሰራጨት ጀመሩ፡፡ በዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ከፊደላት ጋር ተዋወቁ፡፡ ይህ ተግባራቸው በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ቢደናቀፍባቸውም ከወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ኃይል መባረር በኋላ ማተሚያ ቤቱንም በአዲስ መልኩ በማጠናከር ‹‹ሀ ሁ … እውቀት ይስፋ … ድንቁርና ይጥፋ … ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ … ›› ብለው ጽሑፎችን ማሳተምና ማሰራጨት ቀጠሉ፡፡ በዚህ ስራቸውም ትምህርትን በመላ ኢትዮጵያ ለማዳረስና መሃይምነትን ለማጥፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ ዘመናዊ የሕትመት መሳሪያዎችን ከውጭ በማስመጣት ስራቸውን አስፋፉ፡፡ ‹‹ሀ ሁ››ን፣ ‹‹አቡጊዳ››ንና ‹‹መልዕክተ ዮሐንስ››ን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ300 በላይ መፅሐፍትን ማዘጋጀትና ማሳተም ችለዋል፡፡ የፊደል ገበታን ቀርፀው መሃይምነትን ለማጥፋት ካበረከቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ በአርበኝነት ትግላቸው ላደረጉት ተጋድሎ የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ከእፅዋት የቀለም ዱቄት ቀምመውና በጥብጠው፣ ከመቃ እንጨት ብዕር ቀርጸው በወረቀት ላይ ፊደል በመፃፍ በካርቶን ላይ እየለጠፉ በማቅረብ ሚሊዮኖችን ከመሃይምነት ያወጡና የእውቀትን ብርሃን የፈነጠቁ ታላቅ የአገር ባለውለታ ናቸው፡፡
ግንቦት 27 ቀን 1983 ዓ.ም – መላውን አዲስ አበባን ያስደነገጠው፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው፣ በርካቶችን ያቆሰለው … የጎተራ ጦር መሳሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤት ፍንዳታ ተከሰተ፡፡ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ከአንድ ሳምንት በኋላ የተከሰተው ይህ ፍንዳታ፣ ከጎተራ እስከ ሰሜን ሆቴል የተሰማ … ከአቃቂ እስከ ኮተቤ ድረስ ቀልብን የገፈፈ ክስተት ነበር። ከኢትዮጵያ ጋር ልዩ ቁርኝት የነበረው ታዋቂው ኬንያዊ የፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን (Mohamed “Mo” Amin) በፍንዳታው አንድ እጁን አጥቷል፡፡ ጆን ማታይ የተባለው ባልደረባው ደግሞ ለሕልፈት ተዳርጓል፡፡
በወቅቱ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ለፍንዳታው ጣቱን በደርግ ሰዎች ላይ ቀሰረ። ‹‹ማከማቸውን ሆን ብለው ያፈነዱት ‹የደርግ ርዝራዦች› ናቸው›› አለ። የሆነው ሆኖ የጎተራው ፍንዳታ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ ካለው የግንቦት ወር ክስተቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
ግንቦት 29 ቀን 1838 ዓ.ም – የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (Young Men’s Christian Association – YMCA) ተመሰረተ፡፡ በእንግሊዛዊው ሰር ጆርጅ ዊልያምስ የተመሰረተውና ዋና መስሪያ ቤቱ ጀኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ውስጥ የሆነው ይህ ማኅበር፤ በጤናማ አካል፣ አዕምሮና መንፈስ የዳበረ ትውልድ/ኅብረተሰብ የመፍጠር ዓላማ አለው፡፡
Add comment