የካቲት 8 ቀን 1889 ዓ.ም – በኩፊት፣ በዶጋሊ፣ በጉንደት፣ በጉርዓ፣ በሰሀጢ፣ በመተማ፣ በዓድዋና በሌሎች አውደ ውጊያዎች ከወራሪዎች ጋር ተፋልመው አንፀባራቂ ድሎችን ያስመዘገቡት ኢትዮጵያዊው ስመ ጥር የጦር መሪና አስተዳዳሪ ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባ ነጋ) አረፉ፡፡
የካቲት 8 ቀን 1889 ዓ.ም – ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ባንክ (አቢሲንያ ባንክ) መርቀው ከፈቱ፡፡ ከምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላም ንጉሠ ነገሥቱ በቁጠባ ደብተራቸው የጠገራ ብር በባንኩ በማስቀመጥ የአዲሱ ባንክ ሁለተኛ ደንበኛ ሆኑ። የመጀመሪያው የባንኩ ደንበኛ በወቅቱ ለጉብኝት አዲስ አበባ ገብቶ የነበረው እንግሊዛዊው አርኖልድ ሄንሪ ሳቬጅ ላንዶር (Arnold Henry Savage Landor) ነበር፡፡
የካቲት 8 ቀን 1954 ዓ.ም – የንጉሰ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባለቤት የነበሩት እቴጌ መነን አስፋው አረፉ፡፡ እቴጌ መነን ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለነፃነት ተጋድሎው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንም አቋቁመዋል፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡
የካቲት 8 ቀን 1974 ዓ.ም – ኤርትራን ለመገንጠል ሲንቀሳቀስ የነበረውንና ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ/ሻዕቢያ የተባለውን አማፂ ቡድን የመደምሰስ ዓላማ የነበረው እንዲሁም የሺዎችን ሕይዎት የቀጠፈውና ቢሊዮን ብሮችን የፈጀው ‹‹የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ›› ተጀመረ፡፡ ከዛሬ 38 ዓመታት በፊት (የካቲት 8 ቀን 1974 ዓ.ም) ነበር፡፡ይህ ቡድን በአሁኑ ወቅት ስያሜው ወደ ‹‹ህዝባዊ ግንባር ንዴሞክራሲን ፍትሕን/ህ.ግ.ደ.ፍ›› የተቀየረ ሲሆን የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ነው፡፡
የካቲት 10 ቀን 1883 ዓ.ም – በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው መኮንን ተወለዱ፡፡ ራስ ቢትወደድ መኮንን ተፈሪ መኮንን (በኋላ አፄ ኃይለሥላሴ) አልጋ ወራሽ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል፡፡ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በአርበኝነት ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ታዋቂ ደራሲም ናቸው፤በስነ ልቡና፣ በታሪክና በሳይንስ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሐፍትን ጽፈዋል፡፡ ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት መውደቅ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የልጅ እንዳልካቸው አባት ናቸው፡፡
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም – በኢትዮጵያ የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር ኃላፊ የነበረውን ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒን ለመግደል ለተሰነዘረው ጥቃት በተወሰደ የበቀል እርምጃ ከ30ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ተጨፈጨፉ፡፡ ጭፍጨፋው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የዘለቀ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነበር፡፡ ግራዚያኒን ለመግደል ቦምብ የወረወሩት ግለሰቦች አብርሃ ደቦጭ እና ሞገሥ አስገዶም ነበሩ፡፡
የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም – ስመጥሩ ደራሲ፣ አርታዒና ጋዜጠኛ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ‹‹ሌሊቱም አይነጋልኝ››፣ ‹‹ትኩሳት››፣ ‹‹አምስት ስድስት ሰባት››፣ ‹‹ሰባተኛው መልአክ››፣ ‹‹የፍቅር ሻማዎች››፣ ‹‹ስምንተኛው ጋጋታ››፣ ‹‹እነሆ ጀግና››፣ ‹‹እግረ-መንገድ›› የተሰኙና ሌሎች መጽሐፍትንና መጣጥፎችን ጽፏል፡፡
የካቲት 14 ቀን 1957 ዓ.ም – የጥቁሮች መብት ተሟጋቹ ማልኮም ኤክስ (Malcolm X) ተገደለ፡፡ ማልኮም ከስመ ጥር ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መካከል አንዱ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
Leave a reply