የካቲት 30 ቀን 1888 ዓ.ም – በዓድዋ ጦርነት ወቅት የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፍራንቼስኮ ክሪስፒ ከስልጣን ለቀቁ፡፡ ጠቅላይ ሚስትሩ ከስልጣናቸው የለቀቁት የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ዓድዋ ላይ በኢትዮጵያ ጦር ከተሸነፈ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ የጥቁር አገር ጦር የኃያል ነጭ መንግሥት ጦርን አሸንፎ ስለማያውቅና የኢትዮጵያ ድል በአውሮፓውያን ዘንድ ድንጋጤን በመፍጠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒና ካቢኔያቸው ከፍተኛ ጫናና ወቀሳ ደርሶባቸው ነበር፡፡
መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም – ለንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው የመተማ (ጋላባት) ጦርነት ተካሄደ፡፡ ደርቡሾች (መሐዲስቶች) በዘኪ ቱማል እየተመሩ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት ብዙ ጥፋት ያደርሱ ነበር፡፡ ከጣሊያኖች ጋር ውጊያ ላይ የነበሩት ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛም ደርቡሾች በተለይም በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጥፋት ለመበቀልና የአገራቸውን ድንበር ለማስከበር ‹‹መጣሁ ጠብቀኝ! እንደ ሌባ አዘናግቶ ወጋኝ እንዳትል!›› የሚል መልዕክት ወደ ዘኪ ቱማል ላኩና ብዛት ያለውን ጦራቸውን ይዘው ወደ መተማ ዘመቱ፡፡
መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ ከረፋዱ በሦስት ሰዓት ላይ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ልክ እንደ ተራ ወታደር መሐል ገብተው ሲዋጉ ዋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በርትተው እየተዋጉና ምርኮ በመያዝ ላይ ሳሉ በድንገት ከጠላት ወገን የተተኮሰ ጥይት ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስን አቆሰለቻቸው፡፡ የንጉሰ ነገሥቱን መቁሰል ያየው ሰራዊታቸውም ተደናግጦ መሸሽ ጀመረ፡፡
መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም – መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም በተደረገው የመተማ ጦርነት በጽኑ ቆስለው የነበሩት ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ አረፉ፡፡ ደርቡሾችም እየተከታተሉ የንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛን አስክሬን ይዘው አትባራ ወንዝ ዳር ሰፍረው በነበሩት ኢትዮጵያውያን መኳንንትና ወታደሮች ላይ ጥቃት በመፈፀም በማግሥቱ፣ መጋቢት 3 ቀን 1881 ዓ.ም፣ የንጉሰ ነገሥቱን ጭንቅላት ቆርጠው ወሰዱት፡፡
አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ኢትዮጵያን ከጥር 1864 ዓ.ም እስከ መጋቢት 1881 ዓ.ም የመሩት ታላቅ ንጉሰ ነገሥት ነበሩ፡፡
መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም – ገና ከለጋ እድሜያቸው ጀምረው ኢትዮጵያን በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገሉትና በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩ ፖለቲከኞች መካከል በጥንካሬያቸውና በአዋቂነታቸው ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፉት ስመ ጥሩ ዲፕሎማት ክቡር ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ተወለዱ፡፡
ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ውክልናና ጥቅም እንድታገኝ ያደረጉት ተጋድሎ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ቀን በባቡር፣ ሌሊት ደግሞ በመርከብ እንዲሁም በአውሮፕላን ያለምንም እረፍት ለበርካታ ቀናት እየተጓዙ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ ደክመዋል፡፡
ገና በወጣትነታቸው በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) የኢትዮጵያ ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ፤ አፋምቦ፣ ኦጋዴን፣ ጋምቤላና ኤርትራን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ከነበሩ ቅኝ ገዢ አገራት ግዛትነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የሰሩት ስራም ታሪክ አይዘነጋውም፡፡
ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከመወከልና ለጥቅሟ ከመሟገት በተጨማሪ፣ እድገት እንድታስመዘግብና የበለፀገች አገር እንድትሆን በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡
Add comment