የካቲት 22 ቀን 1953 ዓ.ም – የሰላም ዘብ (Peace Corps) የተባለው ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ተግባራትን የሚያከናውነውን የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ተቋም ተመሰረተ፡፡ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ የተቋቋመው በ35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆን ፊዝጌራልድ ኬኔዲ ነው፡፡
በዚህ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ላይ የሚሳተፉ አሜሪካውያን ዜጎች ለበጎ ፈቃድ ተግባራቸው ወደሚሄዱባቸው አገራት ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ለሦስት ወራት ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን፤ ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሁም በትምህርት፣ በእርሻ፣ በጤና፣ በወጣቶችና ሴቶች ልማት፣ በቴክኖሎጂና በአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ላይ አተኩረው ከሚሰሩ የግል ድርጅቶች ጋር እየሰሩ ለሁለት ዓመታት ያገለግላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የመርሃ ግብሩ ዓመታዊ በጀት 390 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም – በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር ዓድዋ ላይ ወራራውን የኢጣሊያ ጦር አሸነፈ፡፡ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ እንድትኖርና ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት እንድትሆን ያስቻለ ታላቅና ታሪካው ድል ነው፡፡ ድሉ ጥቁሮች በነጮች ላይ የተቀዳጁት የመጀመሪያው ታላቅ ድል በመሆኑ እስከዛሬም ድረስ መላውን ዓለም እያስደነቀ ቀጥሏል፡፡
የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም – አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ አረፉ፡፡ ማሞ የተወለዱት ጥቅምት 12 ቀን 1923 ዓ.ም. ነው፡፡ የልጅነት ጊዜያቸው በአስቸጋሪ ሁኔታዎች የተሞላ ነበር፡፡
ማሞ ‹‹ፖሊስና እርምጃው›› የተባለው የፖሊስ ሰራዊት ጋዜጣ በ1952 ዓ.ም. ሲቋቋም የመጀመሪያው የጋዜጣው አዘጋጅ ሆነው ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል። በ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ››፣ ‹‹አዲስ ዘመን›› እና በ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› ጋዜጦችና ‹‹የካቲት›› መጽሔት ላይም ሰርተዋል፡፡
ማሞ 53 መጻህፍትን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ወደ አማርኛ በመተርጎም ለአንባቢያን አድርሰዋል። በስለላና በወንጀል ምርመራ ላይ በሚያጠነጥኑ በርካታ የትርጉም ሥራዎቻቸውና ድርሰቶቻቸው የሚታወቁት ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ሥራዎቻቸው ሕዝባዊነትንና ባሕል አክባሪነትን የተላበሱ በመሆናቸው ዘመን ተሻጋሪ ያደርጋቸዋል፡፡ የታሪክ፣ የልብ ወለድና የተውኔት ስራዎቻቸውም ተወዳጅ ናቸው፡፡
ማሞ ውድነህ ገጣሚም ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ከ200 በላይ ግጥሞችን እንደፃፉ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን ለ12 ዓመታት በሊቀመንበርነት አገልግለዋል። ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ የብዕርና ወረቀት ሰው ብቻ አልነበሩም። ተናጋሪ (Public Speaker) እንዲሁም ያመኑበትን ሃሳብ ከመግለፅ ወደኋላ የማይሉ ሰው ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸውና ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀሳባቸውን ለማካፈል ሁሌም ዝግጁ እንደነበሩ የሚውቋቸው ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል። ስለ ሰላምና መከባበር ደጋግመው የሚሰብኩ ሰው ነበሩ፡፡ ይቅርታ ማድረግም የሁሉም ሰው ባሕል ሊሆን እንደሚገባ አበክረው ሲናገሩ ኖረዋል፡፡
አቶ ማሞ በቀድሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሚመራው የእርቅና ሽምልና ኮሚቴ ውስጥ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላምን ለማምጣት ጥረት ካደረጉ ሰዎች መካከልም አንዱ ነበሩ።
የካቲት 25 ቀን 1938 ዓ.ም – አንጋፋው የፊልም ባለሙያ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ተወለዱ፡፡ አባታቸው ገሪማ ታፈረ ታዋቂ ጸሐፊ ነበሩ፡፡ ‹‹ጤዛ›› የተሰኘውን ፊልም በአማርኛ በመስራት ብቃታቸውን በኢትዮጵያውያን የፊልም ታዳሚዎች ዘንድ ያስመሰከሩት ፕሮፌሰሩ፣ በአለም ዓቀፍ ደረጃም እውቅና ያገኙባቸውን በርካታ ፊልሞች ሰርተዋል፡፡
ከፕሮፌሰር ኃይሌ ስራዎች መካከል ‹‹ሳንኮፋ››፣ ‹‹Hour Glass Hour Glass››፣ ‹‹Child of Resistance››፣ ‹‹Bush Mama››፣ ‹‹Wilmington 10 – U.S.A. 10,000››፣ ‹‹Ashes and Embers››፣ ‹‹After Winter ፡ Sterling Brown››፣ ‹‹ Imperfect Journey›› እና ‹‹Adwa፡ An African Victory›› የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ፕ/ር ኃይሌ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በሀዋርድ ዩኒቨርስቲ የፊልም አሰራር ጥበብ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡
የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም – የኢትዮጵያ ጦር ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ድል በማድረግ ካራማራ በተባለው ተራራ ላይ አሸናፊነቱን አወጀ፡፡ ሶማሊያ በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን በመውረር በርካታ ጦርነቶች እንዲነሱ ምክንያት ሆና ቆይታለች፡፡ የዚህ ድርጊቷ አካል የነበረውና በሶማሊያው መሪ ሜጀር ጀኔራል ዚያድ ባሬ የተመራው የ1969 ዓ.ም ወረራ በኢትዮጵያውያን ጀግንነትና በወዳጅ አገራት እርዳታ ሊቀለበስ ችሏል፡፡
Leave a reply