ሰኔ 7 ቀን 1920 ዓ.ም – አርጀንቲናዊው የማርክሲስት አብዮተኛ፣ የነፃነት ታጋይ፣ ሐኪም፣ ደራሲ፣ መምህር፣ ዲፕሎማት፣ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያና የጦር መሪ … ኧርኔስቶ ‹‹ቼ›› ጉቬራ ተወለደ፡፡
በወጣትነት እድሜው የደቡብ አሜሪካ አገራትን ተዘዋውሮ የተመለከተው ‹‹ቼ››፣ በየሀገራቱ የነበረው ድህነትና ኢ-ፍትሃዊነት የላቲን አሜሪካ ሕዝብ ከተጫነበት የጭቆና ቀንበር እንዲወጣ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት አስገደደው፡፡ ‹‹ቼ›› አስቦም አልቀረ፤ በጓቴማላ፣ በኩባ፣ በሜክሲኮ፣ በቦሊቪያ … እየተዘዋወረ ከነፃነት ታጋዮች ጎን ተሰልፎ አምባገነኖችን ተፋልሟል፡፡
ከአሜሪካ ምድርም ወጥቶ ወደ አፍሪካ ተሻገረና ከአልጀሪያና ከኮንጎ የነፃነት ተዋጊዎች ጋር ተገናኝቶ እርዳታ እንዳደረገ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ወደ ሶቭየት ኅብረት፣ ዩጎዝላቪያና ሌሎች ሀገራትም በመሄድ የዘመኑን ማኅበረ-ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ተመልክቷል፡፡
አብዮተኛው ቼ በህዳር 1959 ዓ.ም ቦሊቪያ ዋና ከተማ ላ ፓዝ ሲደርስ፣ የአምባገነኑ ሬኔ ባሬንቶስ ሐገር የመጨረሻ መዳረሻዬ ትሆናለች ብሎ አላሰበም ነበር፡፡ በማርክሲስታዊ ርዕዮተ ዓለም ተከታይነቱና በአብዮተኛነቱ ምክንያት የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ርዕዮተ-ዓለምን ለማጥፋት ላይ ታች ስትል በነበረችው በአሜሪካ እንዲሁም በድህነትና በጭቆና ቀንበር የሚማቅቀውን ሕዝብ ‹‹እያሳመፀብን ነው›› ብለው … እርምጃው ብቻ ሳይሆን ስሙ ጭምር ባስፈራቸው የደቡብ አሜሪካ አምባገነኖች በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ‹‹ቼ››፣ መስከረም 28 ቀን 1960 ዓ.ም ፌሊክስ ሮድሪጌዝ በተባለ ኩባን ከድቶ ለአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ተቋም (CIA) ሲሰራ በነበረና ክሎስ ባርቢ በተባለ የናዚ የጦር ወንጀለኛ ምክርና ጥቆማ በቦሊቪያ ወታደሮች ቆስሎ ተማረከ፡፡
ቀደም ሲል ጓደኞቹ በ‹‹ቼ›› ተዋጊዎች የተገደሉበት ማሪዮ ቴራን የተባለ የ27 ዓመት የባሬንቶስ ወታደር ‹‹ቼ››ን ለመግደል ጥያቄ አቅርቦ ስለነበር ተፈቀደለት፡፡ ቴራንም በዝነኛው አብዮተኛ ላይ ዘጠኝ ጊዜ አከታትሎ ተኮሰበት! የ‹‹ቼ›› እግሮች፣ ቀኝ ትከሻው፣ ክንዱ፣ ደረቱና ጉሮሮው የገዳዩን ጥይቶች ተቀበሉ፡፡ የዝነኛው አብዮተኛ ሕይዎትም አለፈ፡፡
የአብዮተኛው ኧርኔስቶ ‹‹ቼ›› ጉቬራ የረጅም ጊዜ ወዳጅና የትግል ጓድ የነበሩት የኩባው መሪ ፊደል አሌሃንድሮ ካስትሮ ሩዝ (ፊደል ካስትሮ)፣ እ.አ.አ በ1997 በሳንታ ክላራ ከተማ ለወዳጃቸው የመታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምለት አድርገዋል፡፡
እ.አ.አ ከ1957 እስከ 1968 ለአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ተቋም (CIA) ሲሰራ የነበረና በኋላ ደግሞ ከድቶ ኩባ የቀረ አንድ የስለላ ሰው ‹‹በወቅቱ ሲ.አይ.ኤን በዓለም ላይ እንደ ‹‹ቼ›› ጉቬራ የሚያስፈራውና የሚያስጨንቀው ሰው አልነበረም፤ ምክንያቱም ሰውየው ማንኛውንም ዓይነት ትግል ለመምራትና በድል ለማጠናቀቅ ያለው ችሎታ ብቻ ሳይሆን ግርማ ሞገሱም ጭምር ያስፈራ ነበር›› በማለት አሜሪካ ‹‹ቼ››ን ምን ያህል ትፈራው እንደነበር ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
የዝነኛው አብዮተኛ ስም በኢትዮጵያም ታዋቂ ነው፡፡ ‹‹ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ፣ እንደ ሆ ቺ ሚንህ እንደ ቼ ጉቬራ›› ተብሎ እምቢተኝነት ተሰብኮበታል፤ አብዮት ተቀጣጥሎበታል፡፡
ሰኔ 9 ቀን 1715 ዓ.ም ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ፣ የምጣኔ ሀብት ሊቅና ደራሲ አዳም ስሚዝ፤ ሰኔ 9 ቀን 1959 ዓ.ም ጀርመናዊው የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ እንዲሁም ሰኔ 9 ቀን 1963 ዓ.ም አሜሪካዊው ዘፋኝና የፊልም ተዋናይ ቱፓክ ሻኩር ተወለዱ፡፡
ሰኔ 9 ቀን 1955 ዓ.ም – ሩሲያዊቷ ተመራማሪና መሃንዲስ ቫለንቲና ትሬሽኮቫ የመጀመሪያዋ ሴት ጠፈርተኛ በመሆን ወደ ሕዋ ተጓዘች፡፡ ‹‹ቮስቶክ 6›› በተባለ የበረራ ተልዕኮ ወደ ሕዋ የተጓዘቸው ጠፈርተኛዋ ቫለንቲና ትሬሽኮቫ ለዚህ ተግባሯ ከ10 በላይ አገራት የክብር ዜግነት ሰጥተዋታል፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ ሽልማቶችም ከተለያዩ አካላት ተበርክተውላታል፡፡ ትሬሽኮቫ በሩስያ አየር ኃይል የሜጀር ጀኔራል ማዕረግ አላት፡፡ ከጠፈርተኛነቷ ባሻገር ፖለቲከኛም ናት፡፡
ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም – በቀዶ ጥገና ህክምና ዘርፍ የመጀመሪያው ኢትየጵያዊ ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር ዓስራት ወልደዬስ ተወለዱ፡፡
በታዋቂ የውጭ አገራት የሕክምና ሳይንስ ትምህርት ቤቶች የተማሩት ፕሮፌሰር ዓስራት ‹‹የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ስልጣንን አልፈልግም፤ የተማርኩት ሐኪም ሆኜ አገሬን ላገለግል ነው›› በማለት ወገናቸውን አገልግለዋል፡፡
ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ምክንያት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና ትምህርት ቤትን እውን አደረጉ፡፡ የሕክምና ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋምም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡
ፕሮፌሰር ዓስራት በወቅቱ በተደጋጋሚ ወደ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን፤ የሄዱባቸውንም ዘመቻዎች በብቃትና በክብር ለመወጣት በቅተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዶክተር ዓስራት በህክምናው ዘርፍም ‹‹አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል›› እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ፡፡ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴንም አክመዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዓስራት በመንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች ይደርስባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ሐገራቸውን ሳይለቁ ህዝባቸውን ሲያገለግሉ የቆዩና በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ዓስራት ከሐኪምነታቸው በተጨማሪ ስ ጥር ፖለቲከኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ነበሩ፡፡
Leave a reply