መጋቢት 6 ቀን 1936 ዓ.ም – በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተጋደሉትና ደማቅ የጀግንነት ታሪክ የፃፉት ጀግናው አርበኛና ግዛት አስተዳዳሪ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር አረፉ፡፡
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የተወለዱት ኦጋዴን ውስጥ ካልካዩ በተባለ ቦታ ነው፡፡ ለአካለመጠን ከደረሱ በኋላም የኤል ቡር ገዢ በመሆን አገልግለዋል።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል የያዘችውን የረጅም ጊዜ ዓላማ ለማሳካት ባደረገችው ወረራ ወቅት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ጋር ተሰለፉ፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር የጫረችው የወልወል ጠብ (Wal-wal Incident) የተከሰተው ደግሞ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በነበሩበት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ነበር፡፡
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ወልወል ላይ ኢጣሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ትንኮሳ ስትፈፅም ዝም ብለው አላዩዋትም፡፡ የቻሉትን ያህል አፀፋ በመመለስ በፋሺስት ወታደሮችና በቅጥረኛ ባንዳዎች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በወቅቱም የኢጣሊያ መንግሥት ‹‹ዑመር ሰመተር ተላልፎ ይሰጠኝ›› ሲል በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ለፋሺስት የጦር አለቆች ‹‹ከአገሬ አፈር የሚደባልቅ በልጅግ (ጠመንጃ) እና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ!›› በማለት ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረር እንድትታቀብ ደጋግመው ያስጠነቅቁ ነበር፡፡
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በኤል ቡር፣ በሰላቦ፣ በቆራሄ እና በሌሎችም አካባቢዎች ከጠላት ጦር ጋር ተዋግተው ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ በኋላም የጠላት ጦር ኃይሉ እየከበደ ሲመጣ በገርለጉቤው ጦርነት ዑመር ሰመተር በጠላት ስድስት ጥይት ተመተው በመቁሰላቸው በጦርነት ለመሳተፍ ከማችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ። በውጭ አገርና በሀገር ውስጥ በህክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 6 ቀን 1936 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም ሐረር ከተማ ውስጥ በሚገኘው የአብዱ መስጊድ በሙሉ ወታደራዊ ስርዓት ተፈፅሟል፡፡
መጋቢት 7 ቀን 1868 ዓ.ም – በንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር ጉራዕ በተባለ ስፍራ ላይ የግብጽን ጦር ገጥሞ ታላቅ ድል ተቀዳጀ፡፡ በዚህ ውጊያ ላይ የግብፅ ጦር ዋና አዛዡ ኮሎኔል አረንድሮፕን ጨምሮ በርካታ የወራሪው ኃይል አዛዦችና ወታደሮች ተገደሉ፤ግማሹ ተማረከ፤ጥቂቶቹ ብቻ ሸሽተው አመለጡ፡፡
የግብጽ ጦር በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲፈፅም ኖሯል፡፡ በኅዳር ወር 1868 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈፅሞ ጉንደት በተባለ ስፍራ ላይ በተደረገ ጦርነት ኢትዮጵያውያን በግብፆች ላይ አስደናቂ ድል ተጎናፀፉ፡፡ በጉንደቱ ሽንፈት ክፉኛ የተበሳጨውና ያፈረው የግብፅ መንግሥት ሽንፈቱን ለመበቀል ለዳግም ወረራ ተሰናዳ፡፡ በመሐመድ ራቲብ ፓሻ የተመራው የግብፅ ጦር በመጋቢት 1868 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ገጥሞ የለመደውን ሽንፈት ተጎነጨ፡፡
Add comment