አዳማ፡- በአገሪቱ ከሚገኘው 1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የሠራተኞች ቁጥር ውስጥ አካል ጉዳተኞች 5 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ እንደሆኑ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ገለጸ፡፡
የፌደሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጂ እንደገለጹት፤ 7 ነጥብ 2 በመቶ አካል ጉዳተኞች ብቻ ወደ ትምህርት ገበታ ይሄዳሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 8 በመቶው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቴክኒክና ሞያ ተቋማት እንደሚገቡ መረጃዎች ቢያመላክቱም ብዙ ውጣ ውረዶችን ተቋቁመው ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁት እነዚህ ዜጎችም ቢሆኑ ግን ሥራ አያገኙም፡፡ ከዚህ መጠን ውስጥ 12 በመቶው ብቻ ሥራ እንደሚይዙም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በአገሪቱ ከሚገኘው አጠቃላይ የሠራተኛ ቁጥር የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ለማነሱ የሚነሱ በርካታ ተያያዥ ችግሮች ቢኖሩም የብዙኃን መገናኛዎች ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸው ግን ዋነኛውን ቦታ ይይዛል፡፡ ሚድያዎች ለግጭት ተኮር ዘገባዎች ቅድሚያ ከመስጠት አልፈው የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የዕቅዳቸው አካል አድርገው መሥራት ላይም ከፍተኛ ክፍተት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህም በሕብረተሰቡ ውስጥ ከኖረው የተዛባና ኋላቀር አመለካከት ጋር ተዳምሮ አገሪቱ ከአጠቃላይ ገቢዋ ላይ 5 ነጥብ 1 በመቶ እንድታጣ እያደረጋት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም አካል ጉዳተኞች ለመብታቸው የመታገል ባህልን እንዲያዳብሩ ገልፀው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ ሚድያዎች ንቃተ ሕሊናን በማሳደግ ለውጥ የማምጣት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ17 ሚሊየን በላይ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
አቶ አባይነህ ጉጂ
Leave a reply