የካቲት 2 ቀን ዓ.ም – ‹‹አልወለድም›› የሚለውን ዝነኛ መጽሐፍ ጨምሮ በርካታ ተውኔቶችን፣ ድራማዎች፣ ግጥሞችንና ሌሎች የጽሑፍ ስራዎችን ያዘጋጀው ደራሲ አረፈ፡፡
አቤ ጉበኛ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ከ20 በላይ የልብ ወለድ፣ የድራማና የግጥም መጽሐፍትን ያሳተመ ደራሲ፣ ባለቅኔና ገጣሚ ነው፡፡ የጽሑፎቹ ጭብጦች በጭቆና፣ በሙስና፣ በመሃይምነት እና በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ የመንግሥትን አስተዳደር ብልሹት በሚተቹ ስራዎቹ ምክንያት በሹማምንት ጥርስ ተነክሶበት ለእንግልት ተዳርጓል፡፡ ግፍንና ጭቆናን በብርቱ ታግሏል፡፡ ይህ ጠንካራና ደፋር አቋሙም ውድ ሕይወቱን አስከፍሎታል፡፡ ትውልድና መንግሥትን የነቀነቀው ደራሲ፣ ባለቅኔና ገጣሚ አቤ ጉበኛ ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል ብሎ ያመነበትን አስተሳሰቡን ሳይፈራ የፃፈ የስነ-ጽሑፍ ጀግና ነው፡፡
የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም – የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ፣ ‹‹ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለተ ለዳግማዊ ምኒልክ ስይምተ እግዚአብሔር›› ተብለው በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግስት ተቀብተው የንግሥትነት ዘውድ ጫኑ፡፡
በዚሁ ዕለትም የራስ መኮንን ወልደሚካኤል ልጅ የሆኑት ተፈሪ መኮንን፣ ‹‹ራስ ተፈሪ›› ተብለው ታላቁን የሰለሞን ኒሻን ተሸልመውና ለአልጋ ወራሽ የሚገባው ክብርና ስርዓተ-ፀሎት ተደርጎላቸው፣ ‹‹ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን›› ተብለው ተሰየሙ፡፡
ዘውዲቱ ምኒልክና ተፈሪ መኮንን የዳግማዊ ምኒልክ ዙፋን ወራሽ እንደሆኑ የታወቀው ልጅ ኢያሱ ሚካኤል መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ከዙፋኑ በተሻሩበት ዕለት ነበር፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ ያረፉት መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ነው፡፡
የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም – በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ካላቸው ግለሰቦች መካል አንዷ የሆኑት እቴጌ ጣጥቱ ብጡል ኃይለማርያም አረፉ፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከታመሙ በኋላ ስልጣኑን በእጃቸው አስገብተው ፖለቲካውን ለመዘወር ያላመነቱት፤ አዲስ አበባን የመሰረቱት ብርቱዋ ሴት ጣይቱ፣ ይህ ተግባራቸው ከሸዋ መኳንንት ጋር አጣላቸውና ወደ እንጦጦ ማርያም ሄደው እንዲቀመጡ አስወሰነባቸው፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትም በዚያው በእንጦጦ ሳሉ ነው፡፡ ከአብዛኛዎቹ የዳግማዊ ምኒልክ ውሳኔዎች ጀርባ የባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ጠንካራ እጆች ነበሩ፡፡
የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም – ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ የግዛት ባላባቶችን በጦርነት አሸንፈው፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሱ፡፡ ደጃዝማች ካሣ የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም የስሜንና የትግራይ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያምን ካሸነፉ ከሁለት ቀናት በኋላ (የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም)፣ ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሊነግሱባት አስጊጠው ባሰሯት ደረስጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን በጳጳሱ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኑ፡፡ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ነው፡፡
የካቲት 7 ቀን 1936 ዓ.ም – 37ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን ስልጣናቸውን እንዲለቁ ያስገደዳቸውን የወተርጌት ቅሌት (Watergate Scandal) የምርመራ ዘገባ ከሰሩት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ካርል በርንስቴይን ተወለደ፡፡ ካርል በርንስቴይን የምርመራ ዘገባውን የሰራው ቦብ ውድዋርድ ከተባለው ባልደረባው ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡
Add comment